Written by 11:18 pm Perspectives, Reflections, Technology & Digitalization • 2 Comments

በቀላሉ ስራ ለማግኘት ማድረግ ያለባችሁ 10 ቅድመ ግጅቶች፡ በተለይ ደግሞ ለወጣቶች

ኮሌጅ ተመርቆ ከወጣ በኋላም ለስራ ቅጥር እናቱን ወይም አባቱን ሽምግልና የሚልክ በርግጥስ ተምሯል ማለት እንችላለን ወይ? ነው ወይስ ቤተሰብ ነበር ኮሌጅ የገባው? በሌላ መልኩ ደግሞ ስራ እየፈለገ ቤቱ ቁጭ ብሎ የሚያማርር፤ ስራ ለማግኘት የሚያበቁ ዝግጅቶችን የማያደርግ፤ እቅድና ተግባር ሳይኖረው እንዴት ስራ ወደ እሱ ሊመጣ ይችላል?

ከኮሌጅ እንደወጣህ የስራ ኢንዱስትሪው ውስጥ በቀጥታ ስራ ለማግኘት ምንም አይነት ዋስትና የለህም።  ኮሌጅ እያለህ ግን ቀድመህ ብዙ ማስተካከል ትችላለህ ። እናም ስማኝ።

ጊዜው ተቀይሯል፤ ውድድሩ ጠንካራና ዓለማቀፍ ሆኗል። በየትም አለም አንተን ሊቀጥር ወይም የስራ እድል ለመፍጠር ብሎ የስራ ማስታወቂያ የሚያወጣ የለም፤ ያለበትን ችግር እንዲቀርፍለት እንጂ። ስለዚህ ስራ ካጣህ ወይም የተሻለ ስራ መቀየር ካቃተህ በአመዛኙ የአንተ የራስህ ድክመት መሆኑን አምነህ ያለህበትን ሁኔታ ለመቀየር መትጋት ይጠበቅብሃል። እኔ በእርግጠኝነት የምነግርህ ያን ማድረግ እንደምትችል ነው።

ያን በማመንና ልምዴን በመጠቀም ሃሳብህን ለመሰብሰብ እንዲረዳህ እንደሚከተለው አቅርቤልሃለሁ። አንብበውና አሁኑን ወደ ተግባር ቀይረው። የምትወስደውን ጊዜ ያሳጥርልሃል። ቢያንስ የእኔን ያህክል ጊዜ አይወስድብህም።

  • የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ✅

ከትምህርት ስርዓቱ ጀምሮ በኢትዮጵያ ያለው የስራ አስተሳሰብ ድክመት አለበት ። ቀደም ባሉት ጊዜያት በአብዛሃኛው ሰው የሚማረው የመንግስት ስራ ለመቀጠር ነበር። ምክንያቱ ደግሞ በዋናነት ቀጣሪው የመንግስት ተቋም ስለነበር ነው። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ምንም እንኳን ነባራዊ ሁኔታወች ቢቀየሩም የድሮው እንደባህል ሆኖ የትምህርት ስርዓቱም ይሁን ማህበረሰባዊ ባህሉ ባለመሻሻሉ የተነሳ ብዙ ወጣቶች ከስራ ውጭ ሲሆኑ ወይም ስራ ለማግኘት ረጂም ጊዜ ሲወስድባቸው ይታያል።

ምንም እንኳን ኢኮኖሚው የሰራተኛ ያለህ እያለ ቢጮህም ስራና ሰራተኛ በቀላሉ ለመገናኘት አልቻሉም። ስለሆነም የአሁኑ ወጣት እራሱን ከነባራዊ ለውጦቹ ጋር ማራመድ ይኖርበታል። ቢችል የራሱን ፈጠራ ተጠቅሞ ወደ ቢዝነስ መግባት አለበለዚያም የሚማረው ችግር ለመፍታት መሆኑንና አስፈላጊ የሆኑ ልምዶችናን ችሎታወችን ለማዳበር መትጋት አለበት ። ኢንዱስትሪው የሚፈልገው ችግር የሚፈታለትንና አስተሳሰቡም በዛው መጠን የተስተካከለ ትውልድ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። እውቀትህን፤ አቅምህንና ችሎታህን ተጠቅመህ የሆነን ችግር መፍትሄ ለመስጠት እራስክን ካላዘጋጀህ ጊዜህን አታባክን።

ባጭሩ አንተን ወይም አንቺን ለመቅጠር ስራ የሚያወጣ አካል የለም። ችግሩን የሚያግዘው ወይም የሚያቀልለት መፍትሄ ፍለጋ እንጂ። ስራ የሚሰጠኝ አጣሁ ሳይሆን ይሄንን ችግር እፈታለሁ ወይም አቃልላለሁ በሚል አመለካከት ተክታችሁ ተንቀሳቀሱ። በነገራችን ላይ በመንግስት ተቋም በስራ ላይ ያላችሁና ወደ ግሉ ኢንዱስትሪ ለመለወጥ የምታስቡ ሰወችም ይህንን ብትገነዘቡ ይጠቅማችኋል።

  • ኢንዱስትሪውን በአግባቡ መለየት ✅

ቀጥሎም ከትምህርት ዝግጅታችሁና የረዥም ጊዜ ፍላጎታችሁ አንጻር ትኩረት የምታደርጉበትን ሴክተር በአጋባቡና በበቂ ሁኔታ መለየትና መገንዘብ ይኖርባችኋል።  ግብርና፤ ፋይናንስ፤ ኢነርጂ፤ ኮንስትራክሽን፤ትምህርት፤ ቱሪዝም፤ ጤና ወይንስ ሌላ መሆኑን መለየት ማለት ነው። ከዛም ዋና ዋና ተዋናዮችን መለየት ። የመንግስት፤ የግል፤ መንግስታዊ ያልሆነ ወይስ ደቨሎፕመንት ወይም ደግሞ ጀማሪ፤መካከለና፤ግዙፍ፤ የሃገር ውስጥ አለበለያም አለማቀፍ ተቋም መሆኑን መረዳት ። እነዚህ ሁሉም ምንም እንኳን በአንድ ሴክተር ውስጥ ቢሆኑም የየራሳቸው ፍላጎቶች አሏቸው። ተመሳሳይ ሞያ ( ለምሳሌ መሃንዲስ) ፍላጎት ኖሯቸው የሚፈልጉት የባለሞያ ችሎታና አመለካከት በጣም የተለያዬ ሊሆን ይችላል።

  • ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚፈለጉ ሞያዎችን በሚገባ ለይ ✅

ኢንዱስትሪውንና ዋና ዋና ተዋናዮቹን ከለያችሁ በኋላ ፍላጎታቸውን በቅርበት ለማወቅ ጥረት አድርጉ። በዚህ ጊዜ አብዛሃኛው ተቋም ወይም መስሪያ ቤት ዌብሳይት አለው። ዌብሳይታቸውን በማጥናት ፍላጎታቸውን መገንዘብ   አያቅታችሁም። በተጨማሪም በአካል በመገኘት ስለተቋሙ ጠይቁ፤ እወቁ።

ለምሳሌ አንድ ቀላል መንገድ ልንገራችሁ። የስራ ማስታውቂያ ጋዜጦች፤ የድርጅቶች ዌብሳይቶችን ወይም የስራ ማስታወቂያ ቦርዶችን በማንበብ ብቻ እያንዳንዱ ድርጅት ምንና የት አካባቢ ፍላጎት እንዳለው መለየት ትችላላችሁ። ዝርዝር የስራ መጠይቆችን (job description) በመከታተል ፍላጎታቸውንና የሚፈለጉ ሞያዊ ችሎታዎችን መገንዘብ ትችላላችሁ። እዚህ ጋር የግድ ስራው ላይ ማመልከት አይጠበቅባችሁም ግን ማንበብ ይኖርባችኋል። ስለ አንድ ጉዳይ የበለጠ ግንዛቤው የሚኖራችሁ በተደጋጋሚ ጊዜ ስታጠፉ መሆኑን ተረዱ። ዲግሪ ለማግኘት አራት ወይም አምስት ዓመት እንዳጠፋችሁ አትዘንጉ።  

  • ያሉብህን ክፍተቶች በጊዜ ሙላ ✅

እስካሁን ስለ ስራ ያላችሁን አመለካከት ቀይራችኋል፤ አንዱስትሪውን ለይታችኋል እንዲሁም ዋና ዋና ተዋናዮቹንና ፍላጎታቸውን ለይታችኋል፤ እንበል። ከዛም አሁን ባላችሁ እውቀት፤አቅም እና ችሎታ እና እንዱስትሪው በሚፈልገው መካከል ያለውን ልዩነት በመለየት የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ የሚኖርባችሁ ወቅት ላይ ናችሁ። የእውቀት ክፍተት ካለ ተጨማሪ ክላሶችን መውሰድ፤ የችሎታ ክፍተት ካለ እሱን ለመሙላት ጥረት ማድረግና እራስንዎን ማስተካከል ይኖርበዎታል።

  • በቂ ልምምድና ዝግጅት አድርግ ✅

በተለምዶ እውቀት ያለው ሁሉም እንዳለው ሲነገር እንሰማለን።  በእውነታው አለም ግን እውቀት ብቻውን ያን ያህክል ዋጋ የለውም። በተግባር መፈተንና ወደ ችሎታ መቀየር ይኖርበታል። ችግር የሚፈታው ችሎታ፤ይቻላል የሚል  አስተሳሰብና በተግባር እንጂ በእውቀት ብቻ አይደለም። ስለሆነም በተማሩትና በአወቁት ልክ በቂ ልምምድ ማድረግና ችግር ፈቺ መሆንዎን እርግጠኛ መሆን ይጠበቅብዎታል። እውቀት አቅም እንጂ ችግር ፈቺ አይደለም። የአንድ ስራ ማስታወቂያ ላይ የትምህርት ዝግጅት ከብዙ ፍላጎቶች አንዱ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይችላሉ።

ለምሳሌ፤ የኤክሴል እውቀት ቢኖርዎትና ወደ ችሎታ ማሳደግ ቢፈልጉ በአቅራቢያዎ በሚገኝ አንድ መ/ቤት በነጻም ቢሆን በማገልገል ማዳበር ይችላሉ። በሆነ መስሪያ ቤት ተቀጣሪ ከሆኑም ወደ ሌላ ክፍል በመሄድና ተጨማሪ ስራ በመስራት ማዳበር ይችላሉ።

የስራ ልምድዎን፤ የፈቷቸውን ችግሮችና ስኬትዎን በአግባቡ በመመዝገብና በህሊናዎ በማስቀመጥ ምክንያታዊና ተአማኒ የሆነ ሲቪ ማዘጋጀት ይኖርበዎታል። ሲቪዎ ቆሞ ቀር መሆን የለበትም። የእርስዎ ችሎታና ስኪት ሲያድግ አብሮ ማደግ ይኖርበታል።

  • ፕሮፌሽናል ፕሮፋል ገንባ  ✅

አሁን ዓለም የዲጂታል ወይም የበይነ መረብ ጊዜ ነው። የዲጂታል አቅምዎን በመገንባት ከጊዜው ጋር መጓዝ የግድ ነው። ሙያ ነክ ዲጂታል ሲቪ (እንደ LinkedIn አይነት) መገንባት ይኖርብሃል። ዲጂታል ማንነት ( brand) ገንባ። እጅህ ላይ ያለውን ስልክ በንቃትና በአግባቡ ተጠቀምበት።

  • በአካልም ይሁን በኦንላይን ክስተቶች ወይም ሰሚናሮች ላይ መገኘትና ሃሳብህን ማካፈል ልመድ ✅

አሁን ፍላጎትዎን ለማሳካት የሚረዳዎትን ሲቪ ፕሮፋልና ዝግጅት ገንብተዋል። ነገር ግን ወሳኝ ነገር ይቀርወታል። ባህላችን ዝምተኛነትን ያበረታታል። ይሄ ደግሞ በዘመናዊውና በተያያዘው ዓለም የሚያዋጣ አይደለም። ድክመታችን፤ አቅማችንን፤ እውቀታችንን፤ ችሎታችንን፤ ስኬታችንን በሙሉ ልብ መግለጽ መቻል አለብን። ዝምተኛ እንድንሆን ተደርገን ስላደግን ብዙዎቻችን ስለ እራሳችን በሚገባ መግለጽ እንቸገራለን ወይም ችሎታው የለንም። የቋንቋ አመለካከታችንም ሆነ አቅማችን ብዙ ግድፈቶች አሉበት።

እራሱን መግለጽ የሚያቅተው ሰው ደግሞ በስራው ወይም በቀጣሪወች አለም ትልቅ ድክመት ነው። እራሱን መግለጽ የማይችል ሰው እንዴት ምርታችንና አገልግሎታችን ለሌሎች መሸጥ ይችላል የሚል ትልቅ ስጋት አለባቸው። በርግጥ እኔም የምጋራው ስጋት ነው። የግሉ አለም ከመንግስት የሚቆረጥለት ገቢ የለም። እያንዳንዷ ገቢና ወጪ የምትመዘዘው እያንዳንዱ ሰራተኛ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው።

ስለሆነም አስተዳደጋችሁ የወሰናላችሁን ዝምተኛ ባህሪያችሁን ወደ ጎን ብላችሁ እውነታውን አለም ተጋፈጡ። የማዳመጥና የመናገር ችሎታችሁን በእጂጉ አዳብሩ። ተማሪወች እያለን ብዙ የሚናገሩ ልጆች እንደ ጯሂ ነበር የሚቆጠሩት ። በሚገርም ሁኔታ ብዙዎቹ በእውነታው ዓለም የተሻለ ቦታ ላይ ናቸው። በእርግጥ ማዳመጥና መናገር ችሎታ ነው፤ ይሻሻላንም።

ኢትዮያ ውስጥ ብዙ የወጭ ሀገር ዜጎች አሉ። ብዙ ሺህ ስራ አጥ ወጣት ባለበት ሀገር ይሄ መሆን አልነበረበትም። ክፍተቱ ያለው ኢትዮጵያዊያን ላይ ነው። ምክንያቱም እራሳቸውን ዝግጁ ስላላደረጉ። ውድድሩ አለም አቀፍ ነው። የግል ስኬትን በሚገባ መግለጽ ትልቅ ዋጋ እንዳለው በሚቆጠርበት ዓለም የአንተን ስኬት ሌሎች ያውሩልኝ ካልክ የስራ ዓለም አልገባህም ማለት ነው። ቀጣሪዎች ወይም አሰሪዎች ከእያንዳንዱ ስኬትህ ጀርባ ያለውን ውጣ ውረድ የተወጣህበት አግባብና መልካም ጎን ለራሳቸውም አዲሱ ስራ እንደሚጠቅም ማሰባቸው ነው። ስኬትህን አንተ እራስክ መግለጽ አልቻልክም ማለት የሂወትን ውጣ ውረድ ለመወጣት የሚያስችልህ አመለካከት ወይም ችሎታ አልገነባህም ብለው ነው የሚተረጉሙት ።

  • የመሪነት ሚናውን እራስህ ውሰድ ✅

ችግርህንም ይሁን የምትፈልገውን የምታውቀው አንተ ነው። የትና እንዴት መጓዝ እንዳለብህ መገንዘብና አስፈላጊወን ተግባር ማድረግ ያለብህ አንተ እራስህ ነሕ። ሌሎች ቤተሰብም ይሁን ወዳጅ ወይም አሰሪም ይሁን የስራ ባልደረባ መንገድህን የሚያቀል አቅጣጫ ሊጠቁምህ ይችላሉ እንጂ መንገዱን መጓዝ ያለብህ  አንተ ነሕ። ስራ የለም እያልክ ቤትህ ከተቀመጥክ ችግሩ ያንተ ነው እንጂ የማንም አይደለም። ቤትህ ውስጥ ፋብሪካ እስከሌሌ ድረስ ቤት ውስጥ ስለተቀመጥክ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም። ስራ የሚገኝበት ቦታ መገኘት አለብሕ። ወደ ገበያው መሄድ አለብሕ።ስትሄድ ደግሞ ተዘጋጅተህ መሆን አለበት፤አለበለዚያ የምትገዛው ይጠፋብሃል፤ ብትገዛም ውስጥህ የፈለገው ላይሆን ይችላል።

ከዚያም ባለፈ የምትፈልገውን ነገር መጠየቅና ማሳደድ ያለብህ አንተ እራስክ ነህ ። ከይሉኝታ ወጥተህ ከአንተ የተሻሉ ወይም አቅጣጫ ሊጠቁሙህ የሚችሉ ሰዎችን በአክብሮት ጠይቅና ተረዳ።

  • ያሉ እድሎችን አሳድድ  ✅

ከብዙ ድካም፤ ውጣ ውረድ፤ ልምምድና ትጋት በኋል የሚቀርህ አልመህ መተኮስ ነው። ሁሉም ቦታ መርገጥ ጊዜህንና ጉልበትህን ያባክንብሃል። ዒላማህን ጠበብ አድርገህ ተኩስ። እድሎችን ስታገኝ እከሌማ ዘመድ ወይም ገንዘብ አለው እያልክ እራስክን አታስንፍ። ሁልጊዜ ውድድር እንደሆነ እያሰብክ ገንዘብና ዘመድ ያላቸውን ተወዳዳሪወች ጭምረ በስራህ አሸንፋቸው።

Advertisements

የሚፈለገውን በሚገባ በመረዳት አንተ ክፍተቱን እንደምትሞላ በጽሁፍህም ይሁን በአካል ስትገኝ መተማመኛ ስጣቸው። ማንም ቢሆን የተሻለን ሰው ማጣት አይፈልግም። አንዴ ፤ ሁለቴ ወይም ሶስቴ ሞክረህ ባይሳካልህ ከአንተ የተሻለ ዝግጅት ያደረገ ሰው አግኝተው እንደሆነ ለራስህ ንገረውና ለሚቀጥለው እድል እራስክን የተሻለ ዝግጁ አድርግ። ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ሁሉንም በቅደም ተከተል ደጋግማቸው። ደጋግመህ ሞክር፤ በአንድ ወይም በትንሽ ጊዜ ሙከራ ብቻ ወደምትፈልገው መድረስ አትችልም።

  1. አጋጣሚውን ስታገኝ ምን አቅም እንዳለህና ምን ማበርከት እንደምትችል በተገቢው መንገድ ግለጽ ፤ጥያቄ ጠይቅ፤ ተከታተልም ✅

በመጨረሻም ምን አልባትም የኢንተርቪው እድሉን ስታገኝ ሊቀርፉት የሚፈልጉትን ችግራቸውን እንደምትቀርፍላቸው በሚገባ ንገራቸው። ክፍት የስራ ቦታ ያወጡት አንተን ለመቅጠር ወይም የስራ እድል ለመክፈት አለመሆኑን ተረዳና አንተ መፍትሄ እንዳለህ በሙሉ ልብ ንገራቸው። ምንም እንኳን የትምህርት ዝግጅትህና ልምድህ ከሚፈለገው ያነሰ ቢሆንም እንኳን አመለካከትህንና ዝግጅትህን አይተው የተሻለ እድል ሊሰጡህ እንደሚችሉ አስብ። የማታውቀውን በግልጽ አላውቅም ማለት ልመድ። አላውቀውም ማለትህ ሳይሆን መሸፋፈንህ ዋጋ እንደሚያስከፍልህ እወቅ። ያልገቡህ ጉዳዮች ካሉ ወይም ማብራሪያ ከፈለክ ጠይቅ። ከዛም ማመስገንና መከታተልክን አታቁም። አለባበስህን፤ ድምጽህን፤ አነጋገርህንና የሃሳብ ፍሰትህን በሚገባ ሞርደህ ተገኝ። በርግጥ ሁሉም ነገር እውነተኛና በመረጃ የሚደገፍ መሆን አለበት ።  በሌላ አነጋገር ስራ ከመፈለግህ በፊት አንተ እራስክን አግኝ።

#መልካምእድል

Advertisements
  • ለሌሎች አጋራ፤ ይሄን ተጠቅመህ የምትፈልገውን ለውጥ ካሳካህ አሳውቀኝ። ገጼን ላይክ በማድረክ ሌሎች ተመሳስይ ጽሁፎችን አንብብና ተማርባቸው።
  •   Share such contents and experiences so that we focus on the positives.  You can find English insights ate @showingup+

[hfe_template id=’1537′]

     

Spread the love
[mc4wp_form id="5878"]
Close Search Window
Close