✅ ሚዳቋን ተመልከት። ሁሉም ነው የሚያሯሩጣት።
ቡና እየጠጣሁ ትልቅ እስክሪን ቴሌቪዥን መስኮት ላይ አይኔን ጣል አድርጌአለሁ። ጣቢያው ተፈጥሮአዊ የሆኑ ክስተቶችን በማስተላለፍ ላይ ነበር። ቁጥቋጧማ የሆነ ብዙም ወጣ ገባ የሌለበት አካባቢይን ያስጎበኝ ነበር።
እናም በመሃል አንድ ነብር አንዲትን ሚዳቋ እያሳደደ ብቅ አለ። ትንቅንቁ ለረጂም ጊዜ ቀጠለ። የሚገርም ትእይንት ነበረው። የሁሉም ሰው ቀልብ እስክሪኑ ላይ ነበር።
የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ ብለው ፈጣሪያቸውን ሲጠይቁ፡ ነብሩን ጠንክረህ #እሩጥ ሚዳቋዋን ደግሞ ጨክነሽ #አምልጭ አላቸው የሚባል አባባል ከአሁን በፊት በቀልድ መልክ አንብቤ ነበር። የተፈጥሮ ነገር።
ጥሎብኝ ወይም ጥቃት ያለመውደድ ይሆን እንደ ሚዳቋ ያሉ እንስሣት ያለ በቂ መከላከያ የሁሉም ቀለብ መሆናቸውን ሁል ጊዜ ተመሳሳይ ክስተት ስመለከት ውስጤን ጥሩ ስሜት አይሰማውም። ትምህርት ቤት እያለሁ አንድ ጥቃት የማይወድ ጓደኛ ነበረኝ ። አንድ ጉልቤ ነገር ሌላ ምስኪን የሆነን ግለሰብ ሲያስቸግር ቢያጋጥመው ለምስኪኑ ካላገዝኩ ብሎ ብዙ ጊዜ በማይመለከተው ጉዳይ ተፈናክቶ ያውቃል። እኔም የሚዳቋና መሰሎቻቸው ጉዳይ እንደዚያ ነው የሚሰማኝ።
እናም ከብዙ ማሳደድና የማምለጥ ሙከራ በኋላ ሚዳቋዋ እጅ ሰጠች። ነብሮ የሚዳቋዋን ጉሮሮ አንቃ መሞቷን ካረጋገጠች በኋላ በቅርብ እርቀት ለነበሩ ቤተሰቦቿ ምልክት ሰጠች ። ሁሉም በጉጉት ወደሚጠብቁት ምግባቸው መገስገስ ጀመሩ።
ዳሩ ምን ያደርጋል። አያ ጂቦ ከዬት እንደነበረ ሳይታወቅ ከች አለ እንጂ። አያ ጅቦ ሲደርስ ነብሮ አንድ ጊዜ እንኳን አልነከሰችም ነበር። አለም ክፉ አይደለች። አያ ጂቦ ድካሙ ላይ ምንም ድርሻ ሳይኖረው ጉልቤ ስለሆነ ብቻ መኖው ላይ ወደቀ። ነብሮን አባሮ ሁሉንም ለራሱ አደረገው።
✅ የሚዳቋና የነብሮ ሲገርመኝ ፤ የነብሮና አያ ጂቦ ተጨመረልኝ። ዓለም የጉልቤዎች አይደለች!
ነብሮ በደከመች አያ ጂቦ ሆዷን ሞላች አይደል?
አዎ ሌላ ጊዜ እንደዚያ ሊሆን ይችላል። በቴለቪዢን መስኮት የተመለከትኩት ግን እንደዚያ አልነበረም። በእርግጥ አያ ጂቦና ፈጥነው የደረሱት ጓዶቹ አንድ ሁለቴ የሞተችውን ሚዳቋ ገላ ጎንተል ጎንተል አድርገው ወደ ሆዳቸው ልከዋል። ሶስተኛ ለመድገም ግን እድል ከነሱ ጋር አልነበረችም።
አሁንም ከየት ዱብ እንዳለ ሳይታወቅ ንጉሱ ሰራዊቱን አስከትሎ ከች አለ። አያ ጂቦ በእግር በኩል ፈጥኖ ደራሹ አንበሳ ደግሞ በሌላ በኩል የሞተች ሚዳቋን መጎተት ጀመሩ። አያ ጂቦ ምግቡ ላይ ቢያተኩርም አንበሳ ግን ይበቃሃል አለ። የአንበሳዎች መንጋ ግር ብሎ ሲመጣ በቦታው የነበሩት ሁሉም ጂቦች ጣፋጭ ምግባቸው በአይናቸው እየዞረ እግሬ አውጭኝ ብለው ፈረጠጡ። የአንበሳው መንጋም በብቸኝነትና በአሸናፊነት ኩራት ሆዳቸውን መሙላት ቀጠሉ።
✅ አስቡት ፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን እነ ነብሮ በካሜራ እርቀት ላይ ሆነው እርስ በርስ እየተሻሹ ጭምር ልክ እኔ ቴሌቪዥን እስክሪኑን በማይበት አግባብ የደከሙበትን ጉልቤወች ሲያጣጥሙት ይመለከቱ ነበር። አይገርምም።
ዓለም እንደዚያ ነች ። የደከምክ ሲመስላት ሁሉንም ትወስድብሃለች። ጠንካራ ነን የሚሉ ሃገራት ደክመዋል ብለው የገመቱትን ሃገር በእብሪት ሲያምሱ ማየት የሁል ጊዜ ክስተት ነው። ትልልቅ ኩባንያወች ገንዘብ ስላላቸው ብቻ ግለሰቦች ሂወታቸውን አስይዘው ጭምር የደከሙበትን የስራ ውጤት ያለ አግባብ ሲወስዱ ወይም ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ ሲጥሩ እንዲሁም በህዝብ ገንዘብ ታጥቆ ህዝቡን ምን ታመጣለህ የሚል መንግስት ማየት አድስ ነገር አይደለም።
✅ እንዲያውም አንድ ዘር ሆነን እርስ በእራሳችን የምንባላ ፍጥረቶች ሰዎች ብቻ ሳንሆን አንቀርም።
👉 እናም እልሃለሁ። ዓለም እንደዚህ ነች ። ወጥረህ ስራ። ከዛም ሰበብ ሳትፈልግ በአካል፤ በህሊናና በመንፈስ ጠንክረህ ተገኝ። ያኔ እራስክን ከአንበሳዎች ጎራ ታገኘዋለህ።
✅Join ShowingUp’s Newsletter
[hfe_template id=’1537′]